Skip to main content

መግቢያ

የክልሉ መንግሥት በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ውጤታማ፣ ዘላቂና ተቋማዊ ለማድረግ እንዲሁም የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በተሻለ ሁኔታ ለመፈጸም የሚያስችል ድርጀታዊ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1/2015 መሠረት የፕላንና ልማት ቢሮ ከተቋቋሙት ቢሮዎች አንዱ ነው፡፡ 

በአዋጁ መሠረት ቢሮው የክልሉን የረጅም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ ዕቅዶች ማዘጋጀት፣ አፈፃፀማቸውን መከታተልና መገምገም፣ የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ማዘጋጀትና ማጸደቅ፣ የካፒታል ፕሮጀክቶች ጥናት፣ ክትትልና ግምገማ ማካሄድ፣ የክልሉን የሀብት ግመታና የሀብት ማከፋፈያ ስርዓት ማዘጋጀት እንዲሁም ለምክር ቤት ማቅረብ ዋና ዋና ተግባራቱ ናቸው፡፡ 

እንዲሁም የክልሉን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መረጃዎች መሰብሰብ፣ ማደራጀትና መተንተን፣ የስታቲስቲክስ መረጃ ጥራት ክትትልና ኦዲት ማካሄድ፣ የመረጃ ክፍተት ለማሟላት ጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማከናወን፣ የሥነ-ህዝብ ጉዳዮችን በልማት ዕቅድ አካቶ ማስተባበርና የአምስት ዓመት የሥነ-ህዝብ ፕሮግራም ማዘጋጀት ቢሮው የተሰጡት ተግባራት መካከል ይገኛሉ፡፡ 

እነዚህን ሥልጣንና ተግባራት በብቃት ለመፈጸም ቢሮው በማክሮ ኢኮኖሚ ዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዘርፍ እና በልማት መረጃ አስተዳደርና የሥነ-ህዝብ ጉዳዮች ዘርፍ ተደራጅቶ፣ የተለያዩ ዳይሬክቶሬቶችን በማካተት ድርጀታዊ መዋቅሩን አቋቁሟል፡፡