የቢሮው ሥልጣንና ተግባራት
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ፕላን እና ልማት ቢሮ በክልሉ ም/ቤት የክልሉን አስፈፃሚ መ/ቤቶች እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 199/2015 መሠረት የተቋቋመ ሲሆን በአዋጁ መሠረት ቢሮው የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡፡
1. የክልሉን የረጅም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ ዕቅድ ያዘጋጃል፤ አፈፃፀማቸውን ይከታተላል፤ ይገመግማል፤ ሪፖርት በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው አካላት ያቀርባል፤
2. የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቅፍ ያዘጋጃል፤ለመስተዳድር ምክር ቤት አቅርቦ ያስፀድቃል፤
3. የክልሉን መንግሥት የካፒታል ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት ያካሂዳል፤ይገመግማል፤ያስፀድቃል፤
4. በክልሉ የታችኛውን የአስተዳደር ዕርከን ዓመታዊ የሀብት ማከፋፈያ ቀመር ያዘጋጅል፣ለክልሉ ምክር ቤት እንዲጸድቅ ያቀርባል፣
5. የክልሉን የካፒታል ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ክትትልና ግምገማ ያደርጋል፤ወቅታዊ ሪፖርት በማዘጋጀት አግባብነት ላላቸው አካላት ያቀርባል፣
6. የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አፈፃፀም ጥናት ያካሂዳል፤
7. የክልሉን የልማት ክፍተት እና የመልማት አቅም ጥናት ያደርጋል፤
8. የክልሉን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገፅታ ጥናት ያደርጋል፣
9. የክልሉን የመካከለኛ ጊዜ የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ያዘጋጃል፤ያስፀድቃል፤
10. የክልሉን ዓመታዊ የሀብት ግመታ ሰነድ ያዘጋጃል፤ለክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት በማቅረብ ያስፀድቃል፤
11. የክልሉን የኢኮኖሚ፣የማህበራዊና መልክአ ምድራዊ መረጃዎችን ይሰበስባል፤ያደራጃል፤ትንተና በማድረግ ለተጠቃሚዎች ያሰራጫል፤
12. የክልሉን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ልማት ስርጭትንና የመልክዓ ምድራዊ ገፅታን የሚያሳይ አትላስና ካርታ ያዘጋጃል፤
13. የክልሉ መንግሥት መስሪያ ቤቶች በሥራቸው ኃላፊነት የሚያመነጩትን ስታቲስቲካዊ መረጃዎችን የማሰባሰብ፣ የማደራጀት፣ የመተንተንና ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እንዲሆን የማድረግ እንዲሁም ስታንዳርዱንና ጥራቱን ጠብቆ እንዲዘጋጅ ድጋፍ፣ ክትትል እና ኦዲት ያደርጋል፣ በመረጃዎች ኦዲት ግኝት መሠረት ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል፤
14. የክልሉን የመረጃ ክፍተት ለማሟላት የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ያከናውናል፤
15. የክልሉን የስታቲስቲክስ መረጃ ሥርዓት በማዘመን ለመንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ድጋፍ ይሰጣል፤ሥራውን ያስተባብራል፤ይመራል፤
16. የሥነ- ህዝብ ጉዳዮችን በልማት ዕቅድ አካቶ ከመተግበር አኳያ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ያስተባብራል፤
17. በሥነ -ህዝብ ጉዳዮች የማህበረሰቡንና አመራር አካላትን ግንዛቤ ለማጎልበት የሚያስችሉ የትምህርትና ቅስቀሳ ሥራዎችን ያካሂዳል፤
18. የሥነ ህዝብና ልማት ጉዳዮችን በተመለከተ የጥናትና ምርምር ተግባራትን ያከናውናል፤
19. በየአስተዳደር እርከኑ የሚገኙትን የሥነ ህዝብ ምክር ቤቶችን በማጠናከርና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የአምስት ዓመት የሥነ ህዝብ ፕሮግራም ያዘጋጃል፣ለሥነ ህዝብ ምክር ቤቱ በማቅረብ ያፀድቃል፣ተግባራዊነቱን ይከታተላል፣ይገመግማል አቅጣጫ ያስቀምጣል፤
20. በዕቅድና ፕሮጀክቶች ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዙሪያ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ተግባራዊ ያደርጋል፡፡