የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንነና ልማት ቢሮ ከክልሉ ሳ/እ/ቴ/ቢሮ ጋር በጋራ ያለማዉ ድረ-ገጽ እና የተቀናጀ መረጃ ማሰራጫ ቋት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
ሆሳዕና፦ጥር 19/2018
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፕላንነና ልማት ቢሮ ለተለያዩ የልማትና የዕድገት የመረጃ ምንጭ እንዲሆን ያስለማውን የተቀናጀ መረጃ ማሰራጫ ሲስተም ወይም መረጃ ቋት ስራ አስጀመረ።
የተቀናጀ መረጃ ማሰራጫ ቋቱ በክልሉ ፕላን ልማት ቢሮና በክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ በመተባበር የለማ መሆኑም ተገልጿል።
በመረጃ ቋቱ ስራ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የክልሉ ፕላን ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው፣የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ፣የሁለቱም ቢሮ የስራ ሃላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
የክልሉ ፕላን ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንዳስታወቁት የተቀናጀ መረጃ ማሰራጫ ቋቱ የክልሉን ሁለንተናዊ የልማትና የብልጽግና ጉዞዎች በላቀ ደረጃ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
አገልግሎት መስጠት የጀመረው የመረጃ ቋት ለህብረተሰቡ፣ለአገር ውስጥና ለውጭ ተመራማሪዎችና የምርምር ተቋማት ትክክለኛና ዕውነተኛ መረጃዎች በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያግዝ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
አቶ ዳንኤል አክለውም የመረጃ ቋቱ የቢሮውንና በክልሉ የሚገኙ ተቋማትን መረጃ ለማዘመን፣ብዙ ወጪ የወጣባቸውና የተለፋባቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር መረጃዎች እንዳይጠፉና እንዳይባክኑ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
የመረጃ ቋቱ ስራ መጀመር ለተቋም ግንባታ ስራችን ትልቅ እገዛ አለው ያሉት ቢሮ ሃላፊው ፣ለስራው መሳካት እገዛ ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።
የመረጃ ቋቱ የክልሉን የኢኮኖሚ የማህበራዊና የፖለቲካ ዕቅዶችን በአግባቡ ለመያዝ፣ክልላዊ የመረጃ ክምችትን ለማጎልበትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።
የክልሉን ትክክለኛ መረጃዎች ከአንድ ቋት በቀላሉ ማግኘት የሚያስችለው ይህ የተቀናጀ መረጃ ማሰራጫ የማስፈጸምና የመፈጸም አቅምን ለመጨመር የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረውም አቶ ዳንኤል አስረድተዋል።
ቢሮው ከሌሎች የክልሉ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በመተባበር የሚሰራ እንደመሆኑ ስራ የጀመረው የመረጃ ቋት የሁሉንም ተቋማት መረጃዎች በአግባቡ አካቶ እንደሚይዝም አመላክተዋል።
የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በበኩላቸው፣ ዓለም ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተሸጋገረች በመሆኑ የዌብ ሳይቱ መልማትና ስራ መጀመር ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የመረጃ ቋቱ ክልሉን በስፋት ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝና የተቋሙን ስራዎች ለመሸጥ እንደሚያስችልም አስረድተዋል።
ከቴክኖሎጂ መሸሽ የማይቻልበት ዘመን ላይ ተደርሷል ያሉት ቢሮ ሃላፊው፤ የመረጃ ቋቱ መልማት ለሌሎች የክልሉ ተቋማትም መነቃቃት እንደሚፈጥር አመላክተዋል።
ባለንበት ዘመን የሰዎች ሚና እየቀነሰ ቦታውን ቴክኖሎጂ እየተረከበው እየመጣ ይገኛል ያሉት አቶ ሰላሙ ፣የመረጃ ቋቱ በአግባቡ በመጠቀም የክልሉን ዕምቅ አቅሞች በስፋት ማስተዋወቅና በቂ መረጃ ማደራጀት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሁለቱ ቢሮ ሃላፊዎች የተዘጋጀውን የጋራ መግባቢያና የተቀናጀ ስራ ለመስራት የሚያስችለውን ሰነድ ከፈረሙ በሁላ የመረጃ ቋቱ በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።