የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ሊያሸጋግር ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018(ኢዜአ)፦ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አሠራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ሊያሸጋግር መሆኑን አስታወቀ።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ለማሸጋገር የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢኒስቲትዩት ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ፈርመውታል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ተቋማትን ወደ ዘመናዊ አሰራር ለማሸጋገር ጉዞ ጀምራለች።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴርም አሰራሩን ወደ ዲጂታል ለማሸጋገር ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬው ስምምነትም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
ስምምነቱ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ የልማት ስራዎች በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆናቸውን በዘመናዊ አሰራር ለመከታተል እና ለማረጋገጥ የዲጂታል ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል።
የልማት አስተዳደር ስራዎችና ፖሊሲዎች የሚያመጡትን ውጤት በትክክልኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ግምገማ ለማድረግ ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑንም አስገንዝበዋል
የጥቅል አገራዊ ምርት ዕድገት እና ጥራትን ለመመዘንም ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢኒስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መረጃን ተንትኖ ስራ ላይ ማዋል ዘመናዊ መሰረተ ልማት የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሰል ስራ ላይ የተሰማራው የፕላንና ልማት ሚኒስቴርም ስራው እንዲሳለጥ ፕሮጀክቱን ከተቀመጠው ጊዜ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።