የፌዴራል እና የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ከነገ ጀምሮ እንደሚወያዩ የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።
(ሆሳዕና፦ የካቲት 17/2018) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፌዴራልና የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር በቀጥታ የሚያደርጉትን ውይይት ከነገ ጀምሮ እንደሚያካሂዱ የክልሉ ምክር ቤት አስታውቋል።
መርሐ ግብሩን አስመልክቶ በወልቂጤ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ እንደገለጹት የምክክር መድረኩ በክልሉ የፌዴራል ፓርማ አባላትና የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ቀጥተኛ ውይይት ያደረጋሉ።
በክልሉ የፌዴራል ፓርላማ አባላትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በጋራ የ2018 በጀት ዓመት ሁለተኛ ዙር የህዝብ ውክልና ስራ ያከናውናሉ ብለዋል።
የህዝቡን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመፍታት የውክልና ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባ በመድረኩ ተገልጿል።
በክልሉ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ህዝቡ ላነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት የህዝብ ውክልናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ዋና አፈ ጉባኤዋ አስገንዝበዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየተወከሉበት ምርጫ ክልል በመሄድ ከመራጩ ህዝብ እና በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር ውይይት አድረገው ከህዝቡ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል።
እንደ ክልል በግብርና፣ በከተሞች ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በጤና፣ በትምህርት፣በሰላምና ፀጥታ፣ በፍትህ ስርዓት፣ በኢንቨስትመንት፣በኑሮ ውድነት ቅነሳ፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በፕሮጀክት አፈጻጸም እና በሌሎች ተግባራት ከአስፈጻሚ ተቋማት ጋር በቅንጅት በተሰራው ተግባር ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።
የምክር ቤት አባላቱ የ7ኛ ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ እንዲሆን ብሎም በሌሎች ህዝቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮቾ ላይ እንዲያተኩሩም አሳስበዋል።
ለ10 ተከታታይ ቀናት በሁለቱም ምክር ቤት አባላት የሚደረገው የውክልና ስራ እንዲሳካ የክልሉ ምክር ቤት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
በመድረኩ ቀደም ሲል ህዝቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች የተፈቱበት አግባብና በቀሪ ስራዎች ዙሪያ ከአስፈጻሚ ተቋማት ሃላፊዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ እንደ ክልል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለሌሎች ክልሎችም ተሞክሮ ሊሆኑ የሚገቡ ስራዎች ስለመሰራታቸው ተናግረዋል።
ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በቀጣይም ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ከማህበረሰቡ ጋር ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር የህዝብ ውክልና ተግባርን እውን ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባም ተናግረዋል።