የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በማዘመን የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎች ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተመላከተ። (ሆሳዕና ፣ ጳጉሜ 1/2017)፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና በ2018 ዓ.ም እቅድ ላይ ያተኮረ የምክክር ጉባኤ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ባዩሽ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ተቋሙ የክልሉን የረጅም ፣የመካከለኛና የአጭር ጊዜ እቅድ በማዘጋጀትና ተግባራዊ እንዲደረግ የማድረግ የመገምገምና ግብረመልስ የመስጠት ስራ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በማዘመን የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎችን በመሰብሰብና በማደራጀት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። ከማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ፖሊሲ ጥናቶችን በማካሄድ በክልሉ የሚተገበሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅዶች በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ዶክተር ባዩሽ ተናግረዋል። የስነ-ህዝብ ጉዳዩች የተመለከቱ ጥናቶችን ማካሄድና የህብረተሰብ ግንዛቤ የማሳደግ ስራዎችን በትኩረት ተሰርቷል ያሉት ሀላፊዋ የክልሉን የመልማት አቅም ፣የቁጠባና ኢንቨስትመንት እንዲሁም የመንገድ ኔት ወርክ ጥናቶችን በማከናወን በክልሉ የልማት እንቅስቃሴ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገልፀዋል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን መሰረተ ልማት እና የመንግስት ሀብት ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታመነ ገብሬ እንደገለፁት ቢሮው የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ በክልሉ የመልማት ፍትሀዊነት ጥያቄ እየመለሰ ነው ብለዋል። ጉባኤው በቀጣይ በየደረጃው ወቅታዊ መረጃን መረጃን በወጥነት ማደራጀት ላይ በትኩረት እንዲሰራና ፕሮጀክቶች በወቅቱ እንዲጠናቀቁ በመምከል ጠንካራ ክትትል እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል። ለጉባኤተኞች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አንዮ በዞኑ በርካታ ልማቶች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው ጥናቶች ዞኑ ያለውን የመልማት አቅም በመለየት መጠቀም የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። በጉባኤው የክልል ፣የዞን፣ የልዩ ወረዳ ፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።