የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የየደረጃው አመራሮች በወቅታዊ ክልላዊ ሁኔታዎች ላይ ውይይት እያደረጉ ነው። (ሆሳዕና፦ጥቅምት 08/2018)፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የየደረጃው ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ክልላዊ የፖለቲካና የፀጥታ ሁኔታዎች ላይ በሰባቱም ክላስተሮች፣ ዞኖችና የልዩ ወረዳዎች ውይይት እያደረጉ ነው። የሆሳዕና እና የሀላባ ክላስተር የክልል አመራሮች፤ የሀዲያ ዞን እና የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር፤ የሀላባ ዞን እና የቁሊቶ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የማረቆ ልዩ ወረዳ አመራሮች በጋራ በክልሉ ወቅታዊ የፓለቲካና የፀጥታ ሁኔታ ተወያይተዋል። አመራሮች በጋራ በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግስትና ህዝብ በመቀናጀት ያመጧቸውን ዘርፈ ብዙ ስኬቶች በዝርዝር ተወያይተዋል። ፈጣንና አስደማሚ ዕድገት በክልሉ መመዝገቡ በመድረኮቹ የተነሳ ሲሆን፣ለዚህም በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ህዝብ ሚና ከፍተኛ እንደነበርም ውይይት ተደርጎበታል። በአጠረ ጊዜ ክልሉን የብልጽግና ተምሳሌትና የምርጥ ተሞክሮ መቀመሪያ ለማድረግ የሚያስችሉ ጠንካራ ስራዎች በየደረጃው እየተከናወኑ እንደሚገኙ አመራሮቹ በውይይታቸው አረጋግጠዋል። የክልሉ አመራር ውጤት እያስመዘገበ እንዳለና ህዝቡም በአመራሩ ላይ ዕምነት እያሳደረ ስለመምጣቱም በመድረኮቹ ተነስቷል። የተጀመሩ አጓጊና ተስፋ ሰጪ ስራዎችን በማጠናከር የክልሉን ህዝቦች ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ አመራሩ የተግባር እና የአመለካከት አንድነት መፍጠር እንደሚገባውም ተብራርቷል። በክልሉ በርካታ ድሎች እየተመዘገቡ ቢሆንም አንዳንድ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መሰረት በማድረግ በውስን አካባቢዎች የግል ፍላጎታቸውን በህዝብ ስም ለማሟላት ነጠላ ትርክት የሚነዙ ውዢንብር ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች እንዳሉም በመድረኮቹ ተነስቷል። የክልሉ መንግስት ያደሩ የህዝቦች ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ያደረገውን ጠንካራ ጥረት የገመገሙት አመራሮቹ ፣የክልሉን ሰላም በማረጋገጥ በየአካባቢው የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰሩም አሳውቀዋል። በመድረኮቹ ጠንካራ የፖለቲካ ስራ መስራት፣በቂ ተግባቦት መፍጠር፣የህግ የበላይነት ማረጋገጥ፣የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲን ማጠናከር፣የሰላ ትግል ማድረግ፣ፍጥነትና ፈጠራ የታከለበት ስራ መስራት፣ገዢ ትርክትን በመገንባት የህዝቦች አንድነትን ማጎልበት በድምሩም የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጋራ መግባባት መድረሱን ከፓርቲ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።