Skip to main content
news4

የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የሀገሪቷን ምጣኔ ሀብት በመረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የላቀ ድርሻ እንዳለው ተመላከተ። ሆሳዕና፣ ጥቅምት 13/2018) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጋር በመተባበር ለክልል፣ለዞን እና ለልዩ ወረዳ ለኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ አስተባባሪ ኮሚቴ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሔደ ነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንደገለጹት የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ አላማ የሀገሪቷን ምጣኔ ሀብት በመረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ የደረሰበትን ደረጃ ያመላክታል ያሉት ኃላፊው ተግባሩ የሚመራው ከስታትስቲክስ ባለስልጣን ጋር በመቀናጀት መሆኑን ጠቁመዋል። በክልሉ ከ1ሺ 600 በላይ መረጃ ሰብሳቢዎች ስልጠና ወስደው ወደ ተግባር መግባታቸውን አቶ ዳንኤል አስታውቀዋል። በክልሉ ከ3ሺ በላይ የሆኑ መረጃዎች የሚሰባሰቡባቸው ጣቢያዎችን በመለየት ወደ ስራ ስለመገባቱም ኃላፊው ተናግረዋል። መረጃ የማሰባሰብ ስራ ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ኃላፊው ከዚህ በፊት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በናሙና ላይ የተመሰረተ እንደነበር ጠቁመዋል። አሁን ግን በመላ ሀገሪቱ ገቢ የሚያስገቡ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ተለይቶ በመረጃ ቋት ውስጥ እንዲካተት ያስችላል ብለዋል። ሂደቱ የስታትስቲክስ መረጃን የሚያዘምን እና በዘርፉ ለሚካሔድ ጥናትና ምርምር መነሻ መሆኑንም አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል። በዘርፉ የሚካሔደው የቆጠራ ሂደት ከማንኛውም የገቢ ግብር ጋር የማይገናኝ ነው ያሉት ኃላፊው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ያለበትን ደረጃ እንዲሁም የተፈጠረ የስራ እድል ለማወቅ የሚያስችል ስለመሆኑም ጠቁመዋል። መረጃዎች በተደበቁ ቁጥር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል። ችግሩን ለመፍታት በዘርፉ የሚካሔደው የቆጠራ ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባም አብራርተዋል። በየደረጃው የሚካሔደው የኢኮኖሚ ቆጠራ ስራው ውጤታማ እንዲሆን መገናኛ ብዙሀን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸውም አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል። በመድረኩ የክልል፣የዞን እና የልዩ ወረዳ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል።